»

እንደተቀበልኩት ምህረት እንደቸርነትህ ብዛት እንዳገለግልህ እርዳኝ ጌታ ሆይ ስጠኝ የመንፈስን እሳት"-በዚህ ዌብሎግ እውነተኛው የጌታ ኢየሱስ ባሪያ ተስፋዬ ጋቢሶ ይታወስ ዘንድ ወሰንን።This weblog has been dedicated to Tesfaye Gabiso,the faithful servant of The Lord.

የሚዲያ ጣቢያ



የሚዲያ ጣቢያ


እንደምን ውላችኋል ፤ወንድሞች እና እህቶች ፣ክቡራን እና ክቡራት ፣ቅዱሳን - ህጻናት እና ልጆች።

ይህ የመለኮት ልጆች ሚዲያ ጣቢያ ነው።


የዕለቱ ዝግጅቶች
ዝነኛውና ሠላማዊ-መንፈሳዊው የመለኮት ልጆች የሚዲያ ጣቢያ በዛሬው ዕለት የሚከተሉትን አበይት ዝግጅቶች ይዞላችሁ ቀርቧል።

  • የዕለቱ ዜናዎች
  • ከመንግስት ምክር ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበልን የአቋም መግለጫ
  • ሳምንታዊው የተጓዡ ልቡናችን ዓምድ
  • የአየር ጠባይ ትንተና እና
  • ማስታወቂያዎች ይሆናሉ

(በመጨረሻም መንፈሳዊ ቀልድ እናቀርብሎት ይሆናል)

አሁን የዕለቱን ዜና እናሰማለን ፤በማስቀደምም ዓብይት ርዕሶች
  • የጦርነት ወሬ
  • የፍቅር ጉዳይ
  • የደህንነት አንገብጋቢ ጥሪ

ዜናውን የምናቀርብላቹ ፦ እህታችሁ በእምነት እርምጃ እና ወንድማችሁ ፦ ብላቴናው ወልደመለኮት ነን።

  

የጦርነት ወሬ

-በብላቴናው ወልደመለኮት

የጠላት የማጥቃት  ሙከራ ተቀለበሰ።


በትላንትናው ዕለት ከጠላት ዲያብሎስ መንደር የተወረወረ አገር አቋራጭ ሚሳይል በክርስቲያኖች ሰፈር በመውደቅ ጉዳት ሊያደርስ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ፤የኢየሱስ ስም በተሰኘ ጸረ-ሚሳይል ጥቃቱ በአየር ላይ ሊከሽፍ መቻሉን ብርጋዴር ጄኔራል አምላኪያቸው ከጦር ሜዳ የላኩልን ቴሌግራም ያመለክታል።

ቢሆንም አንዳንድ በጸሎት ያልተጉ ፣በቃል ያልጠነከሩ ፣በመንፈሳዊ ኅብረት ያልተካፈሉ ወገኖች በፍንጣሪ -ማለትም በወሬ፣በአሉ-ቧልታ ፣በሀሜት፣በድካም፣በእንቅልፍ፣በስጋ ሥራ ...ወዘተ መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው ፤ የበጉ ደም በተሰኘ ልዩ መለኮታዊ ዶክተር ታክመው ተፈውሰዋል።

(ሕዝቡም ሁሉ አሜን ክብር ምስጋና ለጌታ ለንጉሱ ይሁን ብሏል።)

***

ፊልድ ማርሻል ድል በመንሳት ሠራዊታቸውን እያተመሙ ነው።


“የሰማይ እና የምድር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ፣የዓለማት ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ፣የነገስታት ሁሉ ንጉስ፣የአማልክት ሁሉ አምላክ ፣የጌቶች ሁሉ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” ሲል የመንግስት ቃል አቀባይ ገለጸ።

(ሕዝቡም ሁሉ አሜን አዎንም እንዲሁም ነውና ክብር ምስጋና ለጌታ ለንጉሱ ይሁን ብሏል።)

“በዚሁ በእግዚአብሔር ልጅ የሚመራ ስፍር ቁጥር የሌለው ጦር ጠላቶቹን ሁሉ እያራደ ፣ተቃዋሚዎቹን እያስወገደ፤ ወዳጆቹን እና አምላኪዎቹን እያዳነ ፣የሚፈሩትን እና ስሙን የሚያከብሩትን ሁሉ ከክፉ እየሰወረ በሚያስፈራ ስልታዊ-ወታደራዊ ዘመቻ እየተመመ ምድርን ሊጎበኝ እየገሰገሰ ነው!”ሲል ብርጋዴር ጄኔራል አጃቢያቸው ተጨማሪ መረጃ ልኮልናል።

(ሕዝቡም ሁሉ አሜን አዎንም ጌታ ሆይ ቶሎ ና! ብሏል።)

***

የፍቅር ወሬ

-ዘጋቢ በእምነት እርምጃው

በመቀጠልም የፍቅር ጉዳይን አስመልክቶ ያሉንን ዜናዎች እናቀርባለን።

 

ፍቅር እሳት አስነሳ

የእህት እህታችን እና የወንድም ወንድማችን ፍቅር ከፍተኛ ደረጃ ደረሰ ተባለ።

ይህም ሊሆን የቻለው እህት እህታችን ከውድ ባሏ  ከወንድም ወንድማችን አስበልጣ እግዚአብሔር አምላኳን መውደድ በመቻሏ ፤ወንድም ወንድማችንም ከእህት እህታችን አስበልጦ እግዚአብሔር አምላኩን ማፍቀር በመቻሉ ነው ሲል ከፍቅር ጉባዔ የተላከልን ዘገባ ያመለክታል።

ይህም መንፈሳዊ ክስተት ከደመናት በላይ በአየር ላይ መንፈሳዊ-እሳታዊ የፍቅር መብረቅ ያስነሳ ሲሆን ፤ይህም የእግዚአብሔር የደስታ መግለጫ ነው ተብሏል።


እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣በፍጹም ሀሳብህ ፣በፍጹም ጉልበትህ ውደድ ተብሎ በሙሴ የእግዚአብሔር ባሪያ ተነግሯልና ይላል የደረሰን መረጃ።
***

የፍቅር ጠላት እጅ ከፍንጅ ተያዘ።


የፍቅር ነኛ ጠላት ማን እንደሆነ ተደረሰበት ሲሉ ጥናታዊ ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር ዊሊያም ኤን አያሌው ገለጹ።


እንደፕሮፌሰሩ ጥናታዊ ግኝት ከሆነ ፍቅርን እንደነቀዝ እየሰረሰረ ፣የሚቦረቡር ተምች በከተማው በሀገሩ የተሰራጨ ሲሆን ይህ ተምች እያንዳንዱ ሰው ቤት ገብቶና ተላምዶ ፣ክብር እና ቦታ ተሰጥቶት በስውር የሰውን ሁሉ ሕይወት ባዶ እያደረገ ነው ሲሉ እኚሁ ምሁር ከከርሰ ምድር ያሰባሰቡት እና በምድር ላይ በሙከራ ያረጋገጡት ግኝት ያመለክታል።ይህ ጥናታቸው በሰማያት መረጅ እና ቅድመ ግኝት የተደገፈ ነው ሲል ይህን ዜና አዘጋጅቶ ከዌስት ኢንድ የላከልን ዘጋቢያችን ያመለክታል። ይህም ተምች ኩብኩባ ገንዘብ ተብሎ ይጠራል ሲሉ እኚሁ ምሁር ጽፈዋል።


ነገር ግን አንዳንድ ምሁራን ገንዘብን መውደድ እንጂ ገንዘብ በራሱ ተምች አይደለም ብለው ብስጭታቸውን በመግለጻቸው ፕሮፌሰሩ -እንዳላችሁ -በማለት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።


እኚሁ ፕሮፌሰር የጥናታዊ ጽሁፋቸውን ክፍል አንድ ሲደመድሙ ፦

“ተምች እና ኩብኩባ አፈርን ለማለስለስ ለጥቂት ይጠቅም ይሆናል፤ዳሩ ግን በተምች እና በነቀርሳ ፍቅር ተነድፈን ፍቅራችን ደፍርሶ ፣ሠላማችን ጠውልጎ ፣የዋህነታችን በልዞ እጣ ፈንታችን ከተምች መንደር እንዳይሆን ጌታ አምላካችን ይታደገን -ይርዳንም” ሲሉ ተማጽነዋል።


***

የደህንነት አንገብጋቢ ጥሪ

በአንድነት እንደተነበበው የዚያን ዕለት በብላቴናው እና በእምነት ።

የደም አዋጅ


በእምነት፡የደም አዋጅ
ብላቴናው፡የሰማ ያሰማ
በእምነት፡ያልሰማ እንዲሰማ

ብላቴናው፡ከጥፋት ከተማ
በእምነት፡ሊያመልጥ የተጠማ

ብላቴናው፡የሕይወትን ውሃ
በእምነት፡እንዲያው ሊጠጣ
ብላቴናው፡ወደ ኢየሱስ ይምጣ።

በእምነት፡የሰማ ያሰማ።

ብላቴናው፡የሞተ እንዲነቃ
በእምነት፡የተኛ እንዲነሳ

ብላቴናው፡ያልሰማ እንዲሰማ

በእምነት፡የመስቀሉን ፍቅር
ብላቴናው፡በኪስህ አትቅበር

በእምነት፡ኃጢያትም በኃይሉ
ብላቴናው፡ሞትም በስልጣኑ 
በእምነት፡ሰይጣን በቀንበሩ
ብላቴናው፡ሞትን ካሸተቱ

በእምነት፡ኢየሱስን ጥራው
ብላቴናው፡ፍቱን መድሃኒቱ።

በእምነት፡የሰማ ያሰማ
ብላቴናው፡ያልሰማ እንዲሰማ
በእምነት፡የሰማ የተኛ
ብላቴናው፡በድጋሚ ይስማ።

***
ሆነም የእረፍት ሰዓት።

እባክዎ ለእረፍት የመረጥንልዎትን መዝሙር ያዳምጡ
(በዚያው እንዳይጠፉ ፣እረፍቱ እንዳለቀ ተመልሰው ይምጡ)

***

የመንግስት ምክር ቤት መግለጫ


አሁን ከእግዚአብሔር መንግስት ተዘጋጅቶ የቀረበልንን የመንግስትን አቋም የሚያንጸባርቀውን መግለጫ እንቀርባለን።

 

በእምነት እርምጃ፦


-የሰሞኑ የአየር ሁኔታ እጅጉን እየቀዘቀዘ በመሆኑ ፍቅችሁ አብሮ እንዳይበርድ ሲል መንግስት አስጠነቀቀ።

ብላቴናው ወልደመለኮት፦


-ማንም የዚህች ኃያል እና ፍጹም ሀገር ዜጋ ቢሆን የሀገሪቱን ክቡር ንጉስ እና የበላይ ጠባቂ ለማየት፣ለመሳለም፣ለመባረክ፣የግል ችግሩን፣ሙግቱን ሁሉ ይዞ ወደ ሀገሪቱ ንጉስ ያለምንም ችግር መምጣት ይችላል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል። 

ክቡር ንጉሰ ንገስቱ እንደሁል ጊዜው እንደዘላለሙ ለዘመናት በሸመገለው ግርማ ሞገሳቸው በሳሎናቸው ዘወትር ተቀምጠው እንግዶችን ይቀበላሉ ፣ያስተናግዳሉ፣ያዳምጣሉ፣ትዕዛዝ ይሰጣሉ ፣ስጦታ ይሰጣሉ፣ስጦታ ይቀበላሉ፣ ለተቸገሩ ይፈርዳሉ ፣ምህረት-ቸርነት ያውጃሉ መጀመሪያ እና መጨረሻ በሌለው ገጸበረከታቸው ይባርካሉ።

ምንም እንኳ ክቡር ነጉሰ-ነገስቱ የሀገሪቱ የበላይ ጠባቂና ባለቤት እጅግ ቸር እና መሀሪ ቢሆኑም ፤ጠባቂዎቻቸው እና አጃቢዎቻቸው ግን ቀልድ የማያውቁ፣የተዳፈረን በእሳት የሚገርፉ ነበልባሎች ስለሆኑ ፤ማንም ወደቤተመንግስት የመጣ በማስተዋል፣በከበሬታ እና በጥንቃቄ የመግባትን እና የመውጣትን ሥርዓት ይፈጽም ተብሏል።


በእምነት እርምጃ፦


እነሆ ውጡ ተራመዱ።መንፈሳችሁ ከምድር ከፍ ይበል።የሞታችሁ ተነሱ።ያንቀላፋችሁ ንቁ።በስጋ እና በደም የታነቃችሁ -ስጋ እና ደምን ትፉት።ቀለል ብላችሁ ውጡ-ግቡ።

ወንጌልን ስበኩ።ነፍሳትን አድኑ።ጠዋት ማታ- በምግብ መብላት ቢሆን፣በውበታችሁ ቢሆን፣በፍቅር ክንውናችሁ ቢሆን ፣በጉልበታችሁ ቢሆን፣በስራችሁ ቢሆን በነገር ሁሉ ጌታን እግዚአብሔርን አምልኩ።

የታመመ ጠይቁ።የታሰረን ጎብኙ።የተቸገረ እርዱ።ከምድር ከፍ በሉ።ለቤተክርስቲያን ሕንጻ ማሰሪያ ከተጠየቃችሁ የምትችሉትን በደስታና በእምነት አድርጉ ሲል የእግዚአብሔር መንግስት የሰሞኑን የአቋም መግለጫ በዚሁ ይቋጫል።

***

የአይር ጸባይ ትንተና፣ የተጓዡ ልቡናችን ዓምድ እና ማስታወቂያዎች ዛሬ የማይቀርቡ መሆኑን በይቅርታዊ ትህትና እናስታውቃለን።

ወይ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ ።

በመጨረሻም ፦ 

 መነፈሳዊ ቀልድ እናቀርላችኋለን ።



___________________________________

*** *** ***
እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ
ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን
የምንሰብከው እርሱ ነው።
 -ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:28

*** *** ***
___________________________________
September 2012.
Elias Aldada

ለዘሬው በዚህ ተፈጸመ ።

ከላይ ያነበቡት ዝግጅት 
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በታላቋ ብሪታኒያ በለንደን ከተማ 
በኪንግስ ክሮስ ዲስትሪክት በምትገኘው የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ኅብረት ቤተክርስቲያን ቀረበ።
***
Directed by :Firew Adinew
Presented By :Bezuye as Beminet Ermija
Elias as Bilatenaw Woldmelekot
Dani  as Metrology man
Written By :Elias Yisehak
***
ክብር ምስጋና ለዘለዓለም ለኢየሱ ይሁን።
እባክዎ “ክብር ለኢየሱስ ይሁን አየን አሸናፊነቱን ኃያል እንደሱ የለም ይንገስ ለዘለዓለም ” የሚለውን መዝሙር ይጋበዙ።

ዋት ቱ ዱ ኔክስት?